ChatCrawlersearch across public Telegram Open the app
E

EHPM - Ethiopian Health Professionals' Movement

сообщение · 2026-06-25 12:51 UTC
E
EHPM - Ethiopian Health Professionals' Movement
‎" ችግሩ ተደጋጋሚ እና ባለድርሻ አካላትም ምላሽ ለመስጠት ዳተኛ ስለሆኑ የትርፍ ሰዓት ሥራ አቁመናል" - የወተራ ራሳ ሆስፒታል ጤና ባለሙያዎች © Tikvah ‎ 👉‎ " ጉዳዩን ወደ ሚዲያ መውሰዳችንን ሰምተው ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ የግንቦት ወር መደበኛ ደመወዝ ብቻ ከፍለዋል" ‎ በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን፣ መልጋ ወረዳ የሚገኘው የወተራ ራሳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት (ዲዩቲ) ክፍያ ተደጋጋሚ አለመከፈልና የደመወዝ መዘግየት ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጋቸው በመግለጽ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጭ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል። ባለስልጣናት በበኩላቸው የካሽ እጥረት ማጋጠሙን አምነው፣ ስራ ግን አልተቋረጠም ሲሉ የባለሙያዎቹን የስራ ማቆም ውሳኔ አስተባብለዋል። ‎ ‎የጤና ባለሙያዎቹ ምን አሉ ? ‎ ወደ 180 የሚጠጉ የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ተፈራርመው ለሆስፒታሉ ባስገቡትና ለቲክቫህ ኢትዮጵያም ባደረሱት የቅሬታ ደብዳቤ፤ መብራትና ኔትወርክ በሌለበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሙያ ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የክፍያ ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ ስላስመረራቸው ስራ ለማቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል። በሆስፒታሉ የ2018 ዓ/ም ሳይጨምር የ7 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፊያ ያላቸው ሰራተኞች ስለመኖራቸው የገለፁት የጤና ባለሙያዎቹ ፦ - ከ2013 (ታህሳስ፣ጥር፣የካቲትና መጋቢት) የ4 ወራት፤ - ከ2014 (ህዳር፣ ታህሳስ) የ2 ወር - ከ2016 የሰኔ ወር በጠቅላይ የ7 ወራት የትርፍ ሰዓት (ዲዩቲ) ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል። " አስቀድሞም ቢሆን የሚከፈልን የትርፍ ሰዓት ክፍያ በአዲሱ የደመወዝ ስኬል ስሌት የተሰራ አልነበረም " የሚሉት የጤና ባለሙያዎቹ፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎችና በሲዳማ ክልል በሚገኙ ሌሎች ሆስፒታሎች ጭምር ክፍያው በአዲሱ ስኬል እየተፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል። " ይህንን አድልዎ ይሁን ብለን በዝምታ ብናልፍም ፣ ከተጠቀሱት የሰባት ወራት ውዝፍ ክፍያዎች በተጨማሪ የ2018 ዓ.ም የግንቦት ወር መደበኛ ደመወዝና የዲዩቲ ክፍያ እስከ ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ ሳይከፈል ቆይቶ ሁኔታውን ይበልጥ አባብሶታል " ሲሉ አስረድተዋል። ‎ ይህን ተከትሎ ሰራተኛው በጋራ በመሰብሰብ ያጋጠማቸውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አቋም መያዙን ጠቅሰዋል። በዚህም መሰረት ከሰኔ 10 እስከ ሰኔ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተጠየቀው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሙሉ በሙሉ የማይፈጸም ከሆነ በማንኛውም የሆስፒታሉ የስራ ክፍል ላይ ሙሉ በሙሉ ስራ ለማቆም እንደሚገደደና ውሳኔያቸውን ለሚመለከተው አካል አስቀድመው ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል። " ይህን ቆራጥ አቋማችንን የተመለከቱት የመልጋ ወረዳ አስተዳዳሪ እና ፋይናስ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ሰራተኞችን ለማወያየት ጥረት አድርገዋል " ያሉት ባለሙያዎቹ " ይህንኑ ለሚዲያም ማሳወቃችንን ሰምተው ቅዳሜ አመሻሽ በ13/10/2018 ዓ.ም መደበኛ ደመወዝ ብቻ አስገብተዋል " ሲሉ ገልጸዋል። ‎ ‎የሆስፒታሉ ሠራተኞች በመነጋገር ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጭ ከሰኞ እስከ አርብ የማታ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ሙሉ ቀን ስራ ማቆማቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል። " መደበኛ ደመወዝ ብቻ እየተከፈለን አሁን ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መቋቋም አንችልም መንግስት ይህን ጉዳይ አስቸኳይ ሊፈታ ይገባል " ሲሉ ጠይቀዋል። ባለድርሻ አካላት ምን ምላሽ ሰጡ ? ‎ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ‎የመልጋ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ በሸንቃ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ጠይቋል። አቶ ታምሩ፣ የሰራተኞች ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን ገልፀው ከዚህ ቀደም ደመወዝ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለየብቻ ይከፈል እንደነበር አስታውሰዋል። ይህን በማስቀረት አንድ ላይ እየተከፈለ የቆየ ቢሆንም በግንቦት ወር የካሽ እጥረት በማጋጠሙ ምክንያት ደመወዝ ብቻ ወደ ሆስፒታሉ አካውንት መላኩን አስታውቀዋል። ‎ ‎የወረዳ አስተዳዳሪው እና ፋይናንስ ኃላፊው የጤና ባለሙያዎችን አነጋግረዋል በቀናት ጊዜ ውስጥ ችግሩ ይፈታል ሲሉም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልፀዋል። የ7 ወራት ውዝፍ ክፊያ ያልተከፈላቸው አሉ ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ " እኔ በቅርብ ነው ወደ ኃላፊነት የመጣሁት ከሶስት ዓመታት በፊት የመንጠባጠብ ሁኔታዎች እንደነበሩ ስምቻለሁ " ብለዋል። ‎ ‎ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመልጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲንግሶ ሕዝቅኤልንም በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሯል። የዘርፉ በጀት በየካቲት ወር ማለቁን ተከትሎ ባለፉት ወራት በብድር ሲከፍሉ መቆየታቸውን ገልፀው የካሽ እጥረት እንዳጋጠማቸውና የግንቦት ወር ደመወዝ በወቅቱ ወደ ሆስፒታሉ አካውንት መላኩን አመልክተዋል። " ሆስፒታሉ ድረስ ሄጄ ከሠራተኞች ጋር ተወያይቻለሁ ከሰኔ ወር ደመወዝና ዲዩቲ ጋር አንድ ላይ እንደሚገባላቸው ተስማምተን ነው የተለያየነው " ሲሉ ተናግረዋል። ‎ ‎ባለሙያዎቹ የትርፍ ሰዓት ስራ ስለማቆማቸው የተጠየቁት ሁለቱም ኃላፊዎች የጤና ጽ/ቤት ኃላፊው እርግጠኛ ባለሆኑ አኳኋን " ስራ ላይ እንደሆኑ ነው የማውቀው " በሚል የገለፁ ሲሆን ፤ የወረዳው አስተዳዳሪ ደግሞ " ከስራ አስኪያጁም ጋር እየተነጋርን ነው ሠራተኞች ስራ አላቆሙም " ብለዋል። ‎ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአከባቢው ነዋሪዎች በኩል ባደረገው ማጣራት፣ ሆስፒታሉ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጪ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑንና ችግሩ በአፋጣኝ እንዲፈታ ጠይቀዋል። ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሀዋሳ ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ/ም

Вся лента · оригинал в Telegram

Open in Telegram Каталог площадок Искать в ChatCrawler

A snapshot of an open public feed from the search index ChatCrawler — “Google for public Telegram”; refreshed as the venue is crawled. Times are UTC.

Public content only, official Telegram API. About · FAQ · What we do not do · Remove a page · Catalog