Adim
" የኤአይ (AI) መተግበሪያዎች የሰው ልጅን የማሰብ እና የመመርመር አቅም ሊያዳክሙ ይችላሉ" - ሮያል ኦብዘርቫቶሪ ግሪንዊች
ለጥያቄዎች እና ውስብስብ ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መተግበሪያዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየበዙ መምጣታቸው የሰው ልጅን የማሰብ አቅም ሊያዳክሙ እንደሚችሉ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ጥንታዊ የሳይንስ ተቋም 'ሮያል ኦብዘርቫቶሪ ግሪንዊች' አስጠነቀቀ።
የተቋሙ ተቆጣጣሪ (ሮያል ሙዚየም ግሪንዊች) ዳይሬክተር ፓዲ ሮጀርስ ለቢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ፤ በኤአይ ላይ የሚኖር " ሙሉ በሙሉ የሆነ ጥገኝነትን " ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዳይሬክተሩ ፥ " በፍጥነት በሚመጡ መልሶች ላይ ብቻ መተማመን፤ ለእውቀት፣ ሙያዊ ብቃት እና ፈጠራ መሠረት የሆኑትን የመጠየቅ እና የመመርመር ልምዶች እንዲጠፉ የማድረግ አደጋ አለው " ብለዋል።
" የሰው ልጅ ለጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በራሱ ጥረት ሲመረምር ያልተጠበቁ ጠቃሚ መረጃዎች ላይ ይደርሳል፤ የኤአይ ፈጣን ምላሾች ግን ይህንን የምርምር ጉዞ ያጠፉታል። ለምሳሌ፦ ቀደምት የከዋክብት አጥኚዎች ያከማቿቸው መረጃዎች ከ150 ዓመታት በኋላ ዛሬ ላለንበት የምድር ጉዞ ትልቅ ሀብት መሆን ችለዋል " ሲሉ አክለዋል።
" እንደ ዊኪፒዲያ ያሉ የቀድሞ መገልገያዎች ተጠቃሚው ወደ ዋናው የመረጃ ምንጭ ሄዶ እውነተኝነቱን እንዲያረጋግጥ ይረዱ ነበር። የኤአይ (AI) መገልገያዎች ግን ዝግጁ መልስ ስለሚሰጡ ሰዎች መረጃን በራሳቸው የመመርመር ልምዳቸው እንዲቀንስ ያደርጋሉ " ብለዋል።
በጽሑፍ፣ በምሥል፣ በቪዲዮ እና በድምጽ የሚሰሩ የኤአይ መገልገያዎች አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ይገኛሉ። ቀላል ረዳት የነበሩት ቻትቦቶች አሁን የሰዎች የቅርብ ወዳጅ እየሆኑ ሲመጡ ምሥል ፈጣሪዎቹ ደግሞ በአደገኛ ፍጥነት እውነተኛ የሚመስሉ ምስሎችን እያመረቱ ነው።
ቴክኖሎጂው ለአሥርት ዓመታት የቆዩ መተግበሪያዎች ውስጥ ያሉ ስህተቶችን በማውጣቱ አድናቆት እየተቸረው ቢሆንም፤ ተጠቃሚዎች በሱ ላይ ብቻ ጥገኞች ከመሆን እንዲቆጠቡ የሚሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ግን በዚያው ልክ እየጨመሩ ይገኛሉ።
ይህ መረጃ የቢቢሲ ነው።
ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ/ም
@tikvahethiopia